በሕግ ማርቀቅ ሂደት የሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር ፍኖተ-ካርታ


                                                                              በሕግ ማርቀቅ ሂደት የሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር ፍኖተ-ካርታ

ማዉጫ

1. መግቢያ.......................................................................................................................................

2. መሰረታዊ መርሆዎች.................................................................................................................

3. ሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር አይነቶች ............................................................................................

4. ህዝባዊ ተሳትፎ ወይም ምክክር የሚደረግባቸዉ ደረጃዎች...........................................................

4.1. ቅድመ ማርቀቅ ተሳትፎ እና ምክክር.............................................................................................. 

4.2. በማርቀቅ ሂደት የሚደረግ ተሳትፎ እና ምክክር................................................................................... 

4.3. የተፅዕኖ ግምገማ ተሳትፎ እና ምክክሮች.........................................................................................

5.የህዝባዊ ተሳትፎ ወይም ምክክር ዕቅድ ስለማዘጋጀት (PUBLIC CONSULTATION PLAN) .......

5.1. የተሳትፎ ወይም የምክክር ዓላማ መግለጫ፣ ወሰን እና ግብ ማዘጋጀት (Statement of Purpose scope, and Objectives) .................

5.2. የማኅበረሰብ አተያይ ትንተና መስራት............................................................................................ 

5.3. የተሳትፎ እና የምክክር ዘዴዎችን መምረጥ (Selecting Consultation Tools)........... .......................

5.3.1. የተሳትፎና የምክክር መድረኮችን ማዘጋጀት.....................................................................

5.3.2. ረቂቅ ሰነዶችን እና ጥናቶችን ለሕዝብ አስተያየት ክፍት ማድረግ...................................................

5.3.3. ረቂቅ ሕጎችን እና ጥናቶችን ለባለድረሻ አካላት በመላክ አስተያየት መሰብሰብ..............................

5.3.4. ረቂቅ ሕጎችን እና ጥናቶችን ለአማካሪ ተቋማት በመላክ አስተያየቶችን መሰብሰብ...................

5.3.5. መደበኛ ያልሆኑ ምክክሮችን ማድረግ...........................................................................................

5.4. የሚያሰራ የጊዜ ሰሌዳ መቅረፅ ................................................................................................... 

5.5. ተሳታፊዎችን መምረጥ............................................................................................................ 

5.6. የሚያሰራ በጀት መመደብ........................................................................................................ 

5.7. ተከታታይ ግምገማ እና ስነዳ..................................................................................................... 

6. በተሳትፎዉ ወይም በምክክሩ ሰዓት ሊደረጉ የሚገቡ ተግባራት .........................................................

7. ተከታታይ አስተያየት መቀበያ ስርዓት መዘርጋት ......................................................................

    1.መግቢያ

ህዝባዊ ተሳትፎና የምክክር ሂደቶች ሕጎችና ደንቦች ግልፅ፣ አሳታፊ፣ በምክክር የዳበሩ እና ላቅ ባለ የጥራት ደረጃ እንዲወጡ የሚያስችሉ መሳሪያዎች ከመሆናቸው አንፃር የሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ ህዝባዊ ምክክሮችን 

በሚመለከት አቅጣጫ ጠቋሚ ፖሊሲዎች ማስቀመጡ ይታወሳል። የአማካሪ ጉባኤው ጽ/ቤት እነኝህን ፖሊሲዎች በተግባር እየሰራባቸዉ ሲሆን ቤቱ በዚህ ሂደት የተመዘገቡ በጎ ተሞክሮዎችን በማጠናከር 

እንዲሁም ሌሎች ተሞክሮዎችን በማከል  ይህን ዝርዝር የሕግ ማርቀቅ ሂደት የሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር ፍኖተካርታ አዘጋጅቷል።

ሕጎች ተፈፃሚ የሚሆኑባቸዉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ሕግ በማዘጋጀት ሂደት ማሳተፍና ማማከር የዴሞክረሲያዊ ስርዓት መገለጫ ከመሆኑም ባሻገር ሕጎች ከፀደቁ በኋላ በማህበረሰቡ ተቀባይነት እንዲኖራቸዉ እና የአፈፃፀም ችግር እንዳይገጥማቸዉ ይረዳል።በሌላ በኩል በጉዳዩ ላይ ልዩ ዕዉቀት ያላቸዉን ባለሙያዎች በማማከር የሚሰበሰቡ ግብዐቶች ሕጎችን በተሻለ ጥራት ለማዉጣት ይረዳሉ። ሰፊ የህዝብ ተሳትፎ ተደርጎባቸዉ የሚወጡ ሕጎች የተለያየ ፍላጎት ያላቸዉ ቡድኖች እና ግለሰቦች እንዲሁም የመንግስት ተቋማት የሚሰጧቸዉን ሀሳቦች በመዉሰድ የሁሉንም ፍላጎት ከግምት ዉስጥ ያስገባ ሕግ ለማዉጣት ይረዳሉ።ይህን ከግምት ዉስጥ በማስገባት ብዙ ሀገራት ወጥ የሕግ አዘገጃጀት የተሳትፎና ምክክር የስነ-ምግባር ደንብ ወይም ኮድ አዘጋጅተዋል። ወጥ የተሳትፎና ምክክር ስነ-ምግባር ደንብ ወይም ኮድ መኖሩ ሁሉም ተቋማት አሳታፊና በምክክር የዳበረ በሆነ መልኩ ሕጎችን እንዲያዘጋጁ ለማድረግ ይረዳል።በተጨማሪም ያለንበት ጊዜ ከፍተኛ ማህበራዊ ነውጦችን እና የፖለቲካ ለውጥን/ሽግግርን ያስተናገደ፣ ሕዝባዊ ተቋማት ላይ ያለው እምነት የተመናመነበት፣የተለያዩ የፖለቲካና ማህበራዊ ውጥረቶች የታዩበት፣እና የማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋትን ተከትሎ የሃሰት መረጃን ጨምሮ የግንኙነት መጠንና ፍጥነት የጨመረበት ከመሆኑ አኳያ በሕግ ማውጣት ሂደት የሚደረግ የተሳትፎና ምክክር ሂደት ልዩ ፈተናዎችን እንደ ሁኔታው ማስተናገድ የሚችል መሆን ይገባዋል።

በኢትዮጵያ የሚኒስቴሮች ምክር ቤት የሕግ ረቂቅ አዘገጃጀት እና አቀራረብ ማንዋል ማንኛዉም ረቂቅ ሕግ ሲዘጋጅ ቅድመ ረቂቅ እና ድሕረ ረቂቅ ምክክሮች ሊደረጉ እንደሚገባ የሚያስገድድ ሲሆን ዝርዝር የተሳትፎና ምክክር ፍኖተ-ካርታ ግን እስካሁን አልተዘጋጀም። በተግባርም እንደየ ተቋማቱ እና የመንግስት ኃላፊዎች ፍላጎት ምክክሮችን በማድረግ ወይም አንዳንዴ ደግሞ በቂ የሕዝብ ተሳትፎ ሳይደረግባቸዉ ሕጎች ሲወጡ ቆይተዋል።በኢትዮጵያ ወጥ እና ዝርዝር የሕግ ማርቀቅ ሂደት የህዝባዊ ተሳትፎና ምክክር ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት የህዝብ ተሳትፎን በማረጋገጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት አይነተኛ መሳሪያ ነዉ። ስለሆነም በኢፌዴሪ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ አማካሪ ጉባኤዉ ብቻ ሳይሆን የመንግስትና ሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት በሕግ ጥናትና ዝግጅት ሂደት ህዝባዊ ተሳትፎና ምክክሮችን ለማዘጋጀት ሊጠቀሙበት የሚችሉት ዝርዝር ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቷል።አማካሪ ጉባኤዉ ለአጭር ጊዜ ለአጭር ጊዜና ያለበጀት የተቋቋመ ከመሆኑ አንጻር ፍኖተ ካርታውን በልምዱ ላይ በመመርኮዝ ደጋግሞ የመከለስና የማሻሻል እድል ያላገኘ ከመሆኑ አንጻር የመንግስትና ሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት ይህን ፍኖተ ካርታ አሻሽለውና አዳብረው እንዲጠቀሙበት /ቤቱ ጥሪ ያቀርባል።     2.መሰረታዊ መርሆዎች

ሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር ተግባሪዎች የተሳትፎና ምክክር ስራዎችን በማቀድና በመተግበር ሂደት ውስጥ ሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር ምን እንደሆኑና ለምን እንደሚተገበሩ በቅጡ መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል።የሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር ጽንሰ ሃሳብና አሰራር የሚመነጨው ከነባር ሊበራል የውክልና ዲሞክራሲ (representative
democracy)
አተገባበር ላይ የታዩ ድክመቶችን ከማረም ጋር የተያያዘ ሙከራ ነው።ከውክልና ዲሞክራሲ ስርዓት ዋና ድክመቶች አንዱ በተወሰነ ግዜ ብቻ የሚካሄዱ ምርጫዎች የመራጮችን ወይም ባጠቃላይ የሕዝቡን ፍላጎት በአግባቡ ማንጸባረቅ አለመቻላቸውና ተመራጮች በሁለት ምርጫዎች መሃል ባለው የጊዜ ክፍተት ለመራጩ ተጠያቂ ያለመሆን አዝማምያ ነው።በዚህና በተያያዥ ምክንያቶች የተነሳ በቁጥር አና ሳየሆኑ የየመደብ፣ የፖለቲካና ቢሮክራስያዊ ልሒቃን በዲሞክራሲያዊ አገዛዝ በማይጠበቅ ደረጃ አንዳንዴም ፀረ-ዲሞክራሲ በሆነ ሁኔታ የሃገሪቱን ሥልጣን ቁጥጥራቸው ስር የመዋል አዝማምያ ሊፈጥሩ ይችላሉ። ሰፊው ሕዝብ በሕግ ሉዓላዊ ነው ቢባልም በተግባር በራሱ መንግስት ላይ ባለቤትነት ማጣቱ የዲሞክራሲን ዋና መርህ የሚንድ ግብዝነት ከመሆኑም ባለፈ ሃገረ መንግስቱን የተቆጣጠሩ ልሒቃን ብዙሃኑ ባልመረጡትና በማይፈልጉት ከዛም አልፎ ብዙሃኑን በሚጎዳ አኳሃን የራሳቸውን ጥቅም ማሳደድ የሚችሉበት ሁኔታም እንደሚፈጥር ይነሳል።ከዚህ ጋር በተያያዘ ከሁለተኛዉ አለም ጦርነት በፊት የነበሩት ዲሞክራሲዎች በልሒቃን ቁጥጥር መዋላቸው እና ይህ ሁኔታ ያስነሳው ሕዝባዊ ቅሬታ ለፋሽዝም መፈልፈልና ለጦርነት መነሳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ይወሳል።

የውክልና ዲሞክራሲ የሃገሩን ዲሞክራስያዊ ባህሪ በመሳት ጥቂት ሰዎች የሚገዙበት ስርዓት (oligarchy) ሆኖ እንዳይቀር እምነት ያጣ ተወካይን ከቦታ የማንሳት፣ ሕዝበ ውሳኔ፣አቤቱታ ወይም ፔትሽን የማቅረብ፣በተለይ በየከተማና ቀዬያዊ የአስተዳደር መዋቅሮች ውስጥ ዜጎች በቀጥታ በመንግስታቸው አሰራር የማሳተፍና እና የመሳሰሉ አሰራሮች ተቀርጸዋል። መልካም ዕድል ሆኖ የኢ... ሕገ-መንግስት እነዚህ የውክልና ዲሞክራሲ ድክመቶችና የማሻሻል ሙከራዎች በቅጡ በታወቁበት ጊዜ በመሆኑ የየውክልና ዲሞክራሲ የተሻለ ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚያደርጉ መዋቅሮች፣መርሆዎችና አሰራሮችን በኢ... ሕገ መንግስትም ተንጸባርቀው እናገኛቸዋለን።

የውክልና ዲሞክራሲን ክፍተቶች ለመጠገን ከተነሱ ንድፈ ሐሳብና አሰራሮች መሃል ተሳትፎአዊ ዲሞክራሲ (participatory democracy) እና ምክክራዊ ዲሞክራሲ (deliberative democracy) ከሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው። የተሳትፎአዊ ዲሞክራሲ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ያላቸው ሃገራት በመደብ፣የፖለቲካና ቢሮክራስያዊ ልሒቃን የማይገባ ቁጥጥር ስር እንዳይወድቁ የፖለቲካ ማህደሩ ወደ ሕዝብ እንዲያጋድል የሚጥር ንድፈ ሐሳብና አሰራር ሲሆን የሕዝባዊ ምክክር በዚህ አስተሳሰብ ስር የዳበረ አሰራር ነው።የውክልና ዲሞክራሲን ተግባራዊ ክፍተቶች ለመሙላት ከሞከሩት ንድፈ ሐሳቦችና አሰራሮች ሌላኛው ምክክራዊ ዲሞክራሲ የሚባለው ሲሆን ተሳትፎ ብቻውን የተሳታፊዎች ግብዓት በሂደቱ ውጤት ላይ ተጽዕኖ ማሳረፉን ስለማያረጋግጥ (ወይም ልሂቃን ተጽዕኖ እንዳይኖረው ሊያደርጉ ስለሚችሉ) የማህበረሰቡ የተለያዩ ክፍሎች በሕግና ፖሊሲ ቀረጻ የሚሳተፉበትን እንዲሁም በሕግና ፖሊሲ ግቦች ላይ መግባባት የሚፈጠርበትን አሰራር ያበረታታል።ሁለቱም አስተሳሰቦች፤ ማለትም የተሳትፎአዊና ምክክራዊ ዲሞክራሲ ንድፈ ሐሳቦች፤ሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር የተወሰነ የፖሊሲ ውጤት ሊያስገኙ ቢችሉም ባይችሉም ተሳትፎና ምክክር መኖሩ ብቻውን የሕብረተሰቡን ባለቤትነት እንደሚያጠናክሩና የሕጎችን ተፈጻሚነት እንደሚያሳልጡም ይስማማሉ።

የሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር እቅድና ትግበራ ሂደት ውስጥ ሌላ ታሳቢ ሊደረግ የሚገባው ጉዳይ የመሳተፍ መብት ከዲሞክራስያዊ መብትነቱ በተጨማሪ የሰብዓዊ መብት አካል መሆኑ ነው።ዜጎች በተለይም ደግሞ ረቂቅ ሕግ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተፅእኖ የሚያሳድርባቸዉ አካላት በፖሊሲና ሕግ ቀረጻ የመሳተፍ መብት እንዳላቸው የኢ... ሕገ መንግስትና [አንቀጽ 8 (3) 89 (6) 35 (3) (6) 43 (2) 92 (3)] አለማቀፍ ሕግ ውስጥ በተለያየ መንገድ የተጠቀሱ ከመሆኑ በተጨማሪ መረጃ ከማግኝት ነፃነት [አንቀጽ29 (3) ()] ጋር ልዩ ግንኙነት አለው።ተሳትፎና ምክክር በተለይ እንደ እድገትና የአካባቢ ደህንነት ያሉ መብቶች ተፈጥሮአዊ ቅጥያ ከመሆናቸውም በተጨማሪ በጾታ፣ በቀለም፣ በዘር፣ በብሄር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት ወዘተ ምክንያት መዋቅራዊ አለመመጣጠን የሚያጋጥማቸው ቡድኖች ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።ሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር ለዲሞክራሲ እድገት ካላቸው ዋጋ አኳያ አንዳንድ በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የተሻለ እድገት ያሳዩ የአፍሪካ ሃገራት ፍርድ ቤቶች (ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካና ኬንያ) በተገቢ ሁኔታ ምክክር ያልተደረገበትን ሕግ ወይም ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድር አስተዳደራዊ ውሳኔን ውድቅ እስከማድረግ ይሄዳሉ።

የሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር የፖለቲካ ስርዓቶች ዲሞክራስያዊነትን ከማጠናከራቸው፣ከሰብዓዊና ዲሞክራስያዊ መብቶች መመንጨታቸውና ለብዙ መብቶች መከበርና መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከማድረጋቸው፣ባለሙያዎች በቀላሉ ሊያውቋቸው የማይችሉ የረቂቅ ሕግና ፖሊሲዎች ማሕበራዊ ተጽዕኖዎችና የሕዝብ አስተያየቶችን የሚያመላክቱ ከመሆናቸው፣እናም ሕጎች ሕዝባዊ ተቀባይነት ኖሯቸው የሃገረ መንግስት አስገዳጅ ሃይል መጠቀም ሳያስፈልግ በውዴታ የሚፈጸሙበትን ሁኔታ ከማበረታታቸው፣እናም የመልካም አስተዳደር መለኪያ ከመሆናቸው አንጻር በሕግ ማርቀቅ ሂደት ውስጥ ሊተዉ የማይችሉ ያደርጋቸዋል።ሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር በሚወጡ ሕጎች ጥራትና ዲሞክራሲያዊነት ላይ ከሚኖራቸው አዎንታዊ አስተዋጽኦ በተጨማሪ ሕብረተሰቡ በፖለቲካ ስርዓቱ ላይ ያለውን አመኔታ ይጨምራሉ።ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት መጀመርያ ላይ ከመሆኗ አንጻር ለሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር ልዩትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል።

ከላይ ከተጠቀሱት ምክንያቶች አንጻር የተሳትፎና ምክክር ተግባሪዎች ግልፅ፣አሳታፊና ምክክር ላይ የተመሰረተ ሕግን ለማዉጣት ወይም አስተዳደራዊ ዉሳኔ ለማሳለፍ የሚከተሉት መርሆዎች ሊሟሉ ይገባል፡-

      o    ማንኛዉም ሕግ ከመፅደቁ በፊት የዜጎችን ዲሞክራስያዊ ተሳትፎ ማጠናከርን ዓላማው አድርጎ በተቻለ መጠን ሰፊና የተለያዩ የሕብረተሰብ አካላትን ያሳተፈ ተሳትፎና ምክክር ሊደረግበት ይገባል፤

      o   ሕጉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ የሚያሳድርባቸዉ አካላት፣የሚመለከታቸዉ የመንግስት አካላት፣ እና የሲቪክ ማኅበራት ሀሳባቸዉን ሊሰጡ ይገባል፤

      o   ረቂቅ ሕግ ተፅእኖ የሚያሳድርባቸዉ አካላት በሚለዩበት ሂደት ከአድልኦ ነጻ የሆነና መዋቅራዊ አለመመጣጠን የሚያጋጥማቸው ቡድኖችን ተሳትፎ ማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፣

      o   ሕግ አርቃቂዎች ተሳታፊዎች የሚሰጧቸዉን አስተያየቶች ረቂቅ ሕጉን ለማዳበር ብሎም ለማሻሻል ሊጠቀሙባቸዉ ይገባል፤

      o   የተሳትፎና ምክክር አዘጋጆች አጠቃላይ ሂደቱን ግልፅ እና ተዐማኒ በሆነ መልኩ ሊያደርጉ ይገባል። ይኸዉም የተሳትፎና ምክክር አዘጋጆች ስለጠቅላላ ሂደቱ፣ስለሕግ ማርቀቁ ሂደት እንዲሁም የሚመለከታቸዉ አካላት የሚሰጡት             አስተያየት እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚዉሉ የሚያሳይ ግልፅ አሰራር መዘርጋት ይኖርባቸዋል፤

      o    የተሳትፎና ምክክር ሂደቱ ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራርን መሰረት ያደረገ ሊሆን ይገባል።አርቃቂዎቹ ተሳታፊዎች የሰጧቸዉ ሀሳቦች በምን ደረጃ ረቂቁን ለማዳበር እንደተወሰዱ የሚያሳይ ሰነድ በቃለ ጉባኤ መልክ በማዘጋጀት             ለተሳታፊዎች ሊገለጹላቸዉ ይገባል።ተሳታፊዎች የሰጧቸዉ ሀሳቦች ረቂቁን ለማዳበር የማይወሰዱ ከሆነ ደግሞ ለምን እንዳልተወሰዱ የሚገልፅ ዝርዝር ማብራሪያ በማዘጋጀት ለተሳታፊዎች ሊገለፅ ይገባል፤

      o   ተሳትፎው ወይም ምክክሩ ከመደረጉ በፊት ለተሳታፊዎች ግልፅ በሆነ መንገድ ጥሪ ሊደረግላቸዉ እና ለዝግጅት በቂ ጊዜ ሊሰጣቸዉ ይገባል፤

      o    ተሳትፎው ወይም ምክክሩ ከመደረጉ በፊት ረቂቅ ሕጉ ወይም ካልተቻለ ለዉይይት የሚቀርቡት ሰነዶች ለተሳታፊዎች ደርሷቸዉ ቀድመዉ ተዘጋጅተዉ ሊመጡ ይገባል፤

      o ተግባሪዎች በሚያዘጋጇቸው የተሳትፎና ምክክር ሂደቶች የተሳትፎአዊ (participatory) እናምክክራዊ (deliberative)
ንድፈ ሐሳቦችን ግንዛቤና ልምድ ታሳቢ ሊያደርጉ ይገባል፤

      o   ተግባሪዎች በሚያዘጋጇቸው የተሳትፎና ምክክር ሂደቶች ውጤታማነትና ቅልጥፍናን ለማዳበር መደበኛ አሰራሮችን የተከተሉ እንዲሆኑ ማድረግ ቢያስፈልግም የተለያዩ ሁኔታዎችን ለሚያስተናግዱ ፈጠራዎችና ሙከራዎች ቦታ              መስጠትም ያስፈልጋል፤

      o   በተቻለመጠንየተሳትፎአዊ (participatory) እናምክክራዊ (deliberative) ንድፈ ሐሳቦችን ግንዛቤና ልምድ ታሳቢ ሊያደርጉ ይገባል፤

      o    የተሳትፎና ምክክር ሂደት በይነመረብ መገናኛ ዘዴዎችን፣መደበኛ ሚዲያና ማሕበራዊ ሚዲያን እና የተለያዩ አዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የተሳትፎና ምክክርን ለማዳበር ሊጥሩ ይገባል፤

      o    ማንኛዉም የተሳትፎ ወይም የምክክር መድረክ ሕጉን በሚፈልጉት መልኩ እንዲፀድቅ ከሚፈልጉ አካላት የገንዘብም ይሁን ሌሎች ተፅዕኖወች ነፃ ሊሆን ይገባል።

            3. ተሳትፎ ወይም ምክክር ሊደረግባቸዉ የሚገቡ ሕጎች

በተለምዶ ህዝባዊ ተሳትፎ የሚደረገዉ በአዋጆች እና ደንቦች ደረጃ ቢሆንም ሌሎች በህዝብ ላይ ተፅዕኖ የሚያስከትሉ አስተዳደራዊ ዉሳኔዎች እና ስትራቴጃዊ ሰነዶችም ህዝባዊ ምክከር ሊደረግባቸዉ ይገባል። በኢትዮጵያ የሚንስትሮች /ቤት የረቂቅ ሕግ አዘገጃጀት እና አቀራረብ ማንዋል ለሚንስትሮች /ቤት የሚቀርቡ ረቂቅ ሕጎች ምክክር እንዲደረግባቸዉ የሚያስገድድ ሲሆን መመሪያዎችን እና አስተዳደራዊ ዉሳኔዎችን አያካትትም። ይሁን እንጅ የፌዴራል የአስተዳደር ተቋማት አዋጅ ቁጥር መመሪያዎች እና አስተዳደራዊ ዉሳኔዎች ከመዉጣታቸዉ በፊት ህዝባዊ ዉይይት እንዲደረግባቸዉ ያስገድዳል። ስለሆነም በኢትዮጵያ አዋጆችን እና ደንቦችን በማዘጋጀት ሂደት ብቻ ሳይሆን መመሪያዎች እና አስተዳደራዊ ዉሳኔዎች ከመዉጣታቸዉም በፊት ምክክር ማድረግ አስፈላጊ ነዉ። በቂ ምክክር ወይም ተሳትፎ ሳይደረግባቸዉ የሚወጡ መመሪያዎችን ወይም አስተዳደራዊ ዉሳኔዎችን ለፍርድ ቤት ቅሬታ በማቅረብ እንዲሻሩ ወይም እንዲስተካከሉ ማድረግ ይቻላል።

         4. የሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር አይነቶች

የሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር ተግባሪዎች በሁሉም ሕግ የማርቅቀ እና ትግበራ ሂደቶች ህዝባዊ ተሳትፎን ዕዉን ለማድረግ የሚያስችሉ የተለያዩ መሳሪያዎች እና ዘዴዎችን መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ አንድን የተሳትፎና ምክክር ዘዴ መጠቀም ማለት ሌሎች ዘዴዎችን ማስቀረት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፡፡ የሕዝባዊ ተሳትፎና ምክክር ተግባሪዎች ሰፊ ግብዐት ለመሰብሰብ እና በህጉ ተጽዕኖ ሊደርስባቸው የሚችሉ ቡድኖችን ለማካተት የሚያስፈልጉ ዘዴዎችን መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ የተሳትፎ ምክክር ዘዴን የመምረጥ ውሳኔ የሚከተሉትን ከግምት ዉስጥ በማስገባት ሊደረግ ይገባል፡-

                   ·  ተሳትፎ እና ምክክር ከሚደረግባቸው ጉዳዮች እና በምክክሩ የሚሳተፉ ሰዎች ብዛት፤

· ጉዳዩ አዳዲስ መፍትሄዎች አፍላቂነት፤

· ምክክሩን ለማድረግ ያለው ጊዜ እና የተመደበው በጀት፤

·  በሚወጣው ህግ ተጽዕኖ ሊደርስባቸው የሚችሉ ሌሎች ሕጎች፤ እና

·  ምክክሩን ለማድረግ የሚያስፈልጉ በእጃችን ያሉ ባለሙያዎች ደረጃ ወይም ተጨማሪ የሚያስፈልጉ ባለሙያዎች እና መረጃ መኖር ይወሰናል።

ተገቢ ዘዴ መመረጡን ለማረጋገጥ፣ ዘዴው የተመረጠበትን ምክንያት ለሚመለከታቸው አካላት ለማስረዳት እና የሚፈለገው ውጤት ዕንደሚሳካ ዋስትና ለመስጠት የምክክር ዘዴን የመምረጥ ስራዎች ምክክር በማዘጋጀት ሂደት በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ከግምት መግባት ይኖርባቸዋል፡፡

ከዚህ በታች በህግ ማርቀቅ ሂደት ውስጥ በተለይ በህጎች፣ በኮዶች ወይም መመሪያዎች አወጣጥ ሂደት ጥቅም ላይ የሚውሉ የተሳትፎና የምክክር ዘዴዎች አጭር ምሳሌ ተቀምጧል፡-

➢ መረጃን ለህዝብ ተደራሽ ማድረግ፡- ማዕከላዊ የሆነ የበይነ መረብ መስመር ላይ የመረጃ ማስተላለፊያ መፍጠር፣ በመንግስት እና በመንግስት አካላት ድህረ ገፆች መረጃዎችን ማሳተም፣ ቴሌቪዠን፣ ሬዲዮ፣ ጋዜጣ እና በመሳሰሉ

➢ ሚድያዎች መረጃ ማሰራጨት እንዲሁም በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መረጃ ማስተላለፊያ፣ጋዜጣ እና ማህበራዊ ሚዲያ መረጃ ማስተላለፍ፣ ወዘተ

   ምክክር ማድረግ፡- የምክክር ጥሪዎችን በበይነ መረብ መስመር የመረጃ ማስተላለፊያዎች  ወይም በመንግስት እና

➢ በመንግስት አካላት ድህረ-ገጾች፣እንደ ቴሌቪዥን እና ጋዜጣዎች ባሉ ሚድያዎች በመጥራት፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች መረጃ ማስተላለፊያዎች ወይም ጋዜጦች፣ በስብሰባዎች፣ በጠረዼዛ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች፣ በዜጎች አማካሪ ቡድኖች፣ በትኩረት ቡድኖች፣ በኢንተርኔት መስመር ላይ በሚደረጉ ውይይቶች በኢሜይል ዝርዝሮች፣ በጽሁፍ አስተያየቶች፣ በባለሙያዎች የመወያያ መድረኮች፣ በህዝባዊ ክርክሮች ማውጣት፣ ወዘተ

  ንቁ ተሳትፎ ማካሄድ፡- የተለያዩ ዘርፎችን ያካተቱ የስራ ቡደኖች፣ የባለሙያዎች ስብሰባዎች፣ የኢ-ሜይል ዝርዝሮች፣ የበይነ-መረብ መስመር ላይ የውይይት መድረኮች፣ ወዘተ ማድረግ

  ምክክር ላይ ማተኮር፡- የዜጎች ስብሰባዎች፤ምክክራዊ ምርጫዎች ወይም ጥናቶች፣ የዜጎች ተነሳሽነት ክለሳ፣ ያልታቀዱ ስልጠናዎች፣ ወዘተ ናቸዉ፡፡

            5. ህዝባዊ ተሳትፎ ወይም ምክክር የሚደረግባቸዉ ደረጃዎች

በሕግ ዝግጅት ሂደት ሕዝባዊ ተሳትፎዎች ወይም ምክክሮች አንድ ጊዜ ብቻ ተደርገዉ የሚጠናቀቁ ሳይሆን ይልቁንም ከቅድመ ማርቀቅ ጀምሮ በተለያዩ ደረጃዎች ሊደረጉ ይገባል።ባለድርሻ አካላት ሕግ እንዲወጣ ሀሳብ ከማመንጨት ጀምሮ ባሉት የሕግ ማርቀቅ ሂደቶች ተሳትፎ ሊያደርጉ ይገባል።

            5.1.ቅድመ ማርቀቅ ተሳትፎ እና ምክክ

ቅድመ ማርቀቅ ተሳትፎ እና ምክክር የሚያስፈልገዉ ሕግ ማርቀቅ ወይም የዳሰሳ ጥናት ስራ ከመጀመሩ በፊት ጉዳዩ ከሚለለከታቸዉ አካላት ጋር በመወያየት በጉዳዩ ላይ ሕግ ማዉጣት ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም የሚለዉን ለመወሰን የሚያስችል የአስፈላጊነት ግብዓት ለመሰብሰብ ነዉ። ግልፅነት እና ተጠያቂነት በሰፈነበት ስርዓት ዉስጥ ማናቸዉም ሕግም ይሁን ፖሊሲ ከህዝብ ተሳትፎ ሊመነጭ የሚገባ ሲሆን ቅድመ ማርቀቅ የህዝብ ተሳትፎ ወይም ምክክሮች ይህን መርህ ለማሳካት አይነተኛ መሳሪያ ናቸዉ። የሕግ ይረቀቅ መመረሪያ ከመሰጠቱ በፊት ሕግ ለማዉጣት ምክንያት የሆነዉን የፖሊሲ ግብ እንዲሁም የታቀደዉን ግብ ለማሳካት ሕግ ማዉጣት የተሻለ አማራጭ መሆኑን ለማረጋገጥ ተሳትፎ ወይም ምክክሮችን ማድረግ ያስፈልጋል። ግልፅ የሕግ ይረቀቅ መመሪያ ለመስጠት ከአርቃቂዉ ተቋም ባለሙያዎች፣ከሌሎች የሚመለከታቸዉ የመንግስት ተቋማት ባለሙያዎች፣እና በዘርፉ ከሚሰሩ ባለሙያዎች ጋር ጠባብ የቅድ መማርቀቅ ምክክሮችማድረግ አስፈላጊ ነዉ። በቅድመ ማርቀቅ ተሳትፎ ወይም ምክክር ሂደት ሕጉን ባመነጨዉ አካል ሕጉን ለማርቀቅ መሰረት የሆነዉ ፖሊሲ፣ የመንግስት አቅጣጫ ወይም ዉሳኔ ቀርቦ ዉይይት ሊደረግበት ይገባል። በኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያዘጋጀዉ የሕግ ረቂቅ አዘገጃጀት እና አቀራረብ የአሰራር ማንዋል የሕግ ረቂቅ ከመዘጋጀቱ በፊት ቅድመ ረቂቅ ምክክር ሊደረግ እንደሚገባ ያስቀምጣል። ስለሆነም በኢትዮጵያ ቅድመ ማርቀቅ ምክክር ማድረግ በአርቃቂዉ ተቋም ፍላጎት የሚደረግ ብቻ ሳይሆን መሟላት የሚገባዉ አስገዳጅ ስነ-ስርዓት ነዉ።

            5.2.በማርቀቅ ሂደት የሚደረግ ተሳፎ እና ምክክር

በማርቀቅ ሂደት የሚደረጉ ምክክሮች እና ተሳትፎዎች አሳታፊ እና ጥራት ያለዉ ሕግን ለማርቀቅ የግድ መደረግ የሚገባቸዉ በአብዛኛዉ የተለመዱ ምክክሮች ናቸዉ። የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ማንዋል አንድ ረቂቅ ሕግ በአማርኛ ከተዘጋጀ በኋላ እንደ ረቂቅ ሕጉ አይነት እና ይዘት ከሚመለከታቸዉ የፌዴራል እና የክልል የመንግስት አካላት፣መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት፣ ከሕዝብ አደረጃጀቶች፣ ከሲቪክ ማኅበራት ድርጅቶች፣ እና ሌሎች የሚመለከታቸዉ አካላት ጋር ምክክሮች ሊደረጉ እንደሚገባ ባስገዳጅነት ተቀምጧል።በዚህ ደረጃ የሚደረጉ ምክክሮች ረቂቁን ለማዳበር የሚረዱ ግብዐቶች ለመሰብሰብ የሚደረጉ በመሆኑ ረቂቅ ሕጉ ለተሳታፊዎች ቀድሞ ደርሷቸዉ ተሳታፊዎች ዝርዝር ሀሳባቸዉን የሚሰጡበት ሂደት ነዉ።

           5.3.የተፅዕኖ ግምገማ ተሳትፎ እና ምክክሮች

አዲስ ሕግ ከፀደቀ እና ስራ ላይ ከዋለ በኋላ ሕጉ ሊሳካ የታሰበዉን አላማ ከማሳካት አንፃር የተመዘገቡ አዎንታዊ ለዉጦችን እና ክፍተቶችን ለመገምገም ምክክሮች ከባለድርሻ አካላት ጋር ሊደረጉ ይችላሉ። እነዚህ የምክክሮች የሕጉን ተፅዕኖ ከመገምገምም ባሻገር ሕጉ ተፈፃሚ የሚሆንባቸዉ አካላት ስለአዲሱ ሕግ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸዉ ለማድሊደረጉ ይችላሉ።በዚህ ሂደት አዲሱ ሕግ ተፈፃሚ የሆነባቸዉ አካላት ሕጉ በተግባር ምን አዲስ ነገሮችን ይዞ እንደመጣ ሀሳባቸዉን ሊገልፁ ይገባል።

              6. የሕዝባዊ ተሳትፎ ወይም ምክክር ዕቅድ ስለማዘጋጀት (Public
Consultation Plan)

ማንኛዉም ዉጤታማ የሕግ ማርቀቅ ስራ የሚጀምረዉ ግልፅ እና የሚያሰራ የትግበራ እቅድ በማዘጋጀት ነዉ። የህዝባዊ ተሳትፎ ወይም ምክክር ዕቅድ ተግባሪዎች ምክክሮችን መቼ፣እንዴት፣እና ከእነማን ጋር ማድረግ እንዳለባቸዉ አቅጣጫ ጠቋሚ ኮምፓስ ሲሆን ሕጎች አሳታፊ እና ጥራት ያላቸዉ ሆነዉ እንዲወጡ ለማድረግ አይነተኛ ሚና ይጫወታሉ። ማንኛዉም የምክክር ወይም የተሳትፎ ዕቅድ የምክክሩን አላማ መግለጫ እና ግብ፣ የተሳታፊዎችን የአመራረጥ መስፈርት፣ ምክክሩ ወይም ተሳፎዉ የሚደረግበትን የጊዜ ሰሌዳ፣ ምክክሩ ወይም ተሳትፎዉ የሚደረግበትን ዘዴ (public
consultation tools)
የሚያስፈልገዉን በጀት፣ የተሳትፎዉ ወይም የምክክሩ ዉጤት ሪፖርት የሚደረግበትን ዘዴ እና አሰራር፣ የሚቀርቡትን ሰነዶች ዝርዝር እና የአቅራቢዎችን ማንነት፣ በፕሮግራሙ የሚኖረዉን ስነ-ስርዓት፣ እንዲሁም የሚመለከታቸዉ አካላት፣ ሚዲያዎች እና ሰፊዉ ማሕበረሰብ ስለረቂቁ ያለዉን አተያይ የሚተነትን ዝርዝሮችን ሊያካትት ይገባል።

             6.1.የተሳትፎ ወይም የምክክር ዓላማ መግለጫ፣ ወሰን እና ግብ ማዘጋጀት (Statement of Purpose scope and Objectives)

ማንኛዉም ሕዝባዊ የምከክር እና ተሳፎ ዕቅድ የሚጀምረዉ የተሳትፎ ወይም የምክክር አላማ፣ ወሰን እና ግብ በግልፅ በማስቀመጥ መሆን አለበት። ግልፅ ዓላማ እና ግብ የምክክሮችን ወሰን ግልፅ የሚያደርግ ሲሆን ምክክሮች ከፈር እንዳይወጡ እና በተፈለገዉ መልኩ ብቻ እንዲመሩ ለማድረግ ያግዛል። የተሳትፎ ወይም የምክክር ዓላማ መግለጫ ሊወጣ የታሰበዉ ሕግ የሚፈታዉን ችግር እና ችግሩን ለመፍታት ሕግ ማዉጣት አስፈላጊ እና የተሻለ አማራጭ ሆኖ መገኘቱን የሚተነትን መሆን አለበት። ብዙ ጊዜ ተሳታፊዎች ከጉዳዩ ጋር የማይገናኙ ሀሳቦችን የሚያነሱ ሲሆን ግልፅ አላማ እና ግብ ካለን ግን የምክከር መሪዎች በእንደዚህ አይነት ሀሳቦች እንዳይጎተቱ ይረዳቸዋል። ባጠቃላይ ማንኛዉም ሕዝባዊ የተሳትፎ እና የምክክር ዕቅድ የሚከተሉትን ዝርዝሮች ያካተተ የአላማ መግለጫ እና ግብ ሊኖረዉ ይገባል፡-

        o  ረቂቅ ሕጉ ሊፈታ ያሰበዉ ችግር ምን እንደሆነ መግለፅ አለበት፤

        o   ሕጉ እንዲረቀቅ ምክንያት የሆኑትን ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች የሚገልፅ መሆን አለበት፤

        o    የረቂቅ ሕጉን አዘገጃጀት ስነ-ስርአት ዝርዝር የሚገልፅ መሆን አለበት፤

        o    ሊደረግ የታሰበዉ ህዝባዊ ተሳትፎ እና ምክክር ትኩረቱን የሚያደርግባቸዉን ጉዳዮች መተንተን፤

  o    በረቂቅ ሕጉ ላይ የሚደረጉትን ምክክሮች ስፋት እና ስርዓት የሚገልፅ መሆን አለበት፤እና

  o    ሕጉን ያረቀቀዉን እና በባለቤትነት የሚመራዉን ተቋም የሚገልፅ መሆን ይኖርበታል።         6.2.የማኅበረሰብ አተያይ ትንተና መስራት

የህዝባዊ ምክክር እና ተሳትፎ ተግባሪዎች ማንኛዉም ህዝባዊ ተሳትፎና ምክክር ከመደረጉ በፊት አዘጋጆች መንግስት እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እና ሰፊዉ ማኅበረሰብ ስለታሰበዉ ሕግ ያለዉ አተያይ ወይም ስሜት ምን እንደሚመስል በመተንተን ጠቅላላ ዕቅዳቸዉን መቃኘት አለባቸዉ።ሊወጣ የታሰበዉ ሕግ የመንግስት ከፍተኛ ሀላፊዎች ድጋፍ ያለዉ እና ከመንግስት የፖሊሲ አቅጣጫዎች ጋር የተጣጣመ መሆኑን ለማረጋገጥ የዉስጥ ግምገማ ማድረግ ያስፈልጋል። በአንፃሩ ባለድርሻ አካላት እና ማኅበረሰቡ እንዲሁም ሚድያዉ ስለሕጉ ያለዉን የአተያይ ደረጃ ቀድሞ መገምገም በተሳትፎና ምክክር ሒደቱ ሊያጋጥሙ የሚችሉ አለመግባባቶችን ለመቀነስ፣ የምናደርጋቸዉን ምክክሮች ብዛት ለመወሰን፣ የተሳታፊዎችን ብዛት ለመወሰን፣የተሳትፎና ምክክሩን ዘዴ ለመወሰን እንዲሁም የማሳወቂያ መሳሪያዎችን ለመምረጥ ያግዘናል። ለምሳሌ ሕጉ አከራካሪ እና ብዙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የሚነካ እንዲሁም የሚድያ እና የመንግስትን ትኩረት የሚስብ ከሆነ ይህን ከግንዛቤ ዉስጥ ባስገባ መልኩ የተሳትፎና ምክክር ዕቅዳችንን መቅረጽ ይኖርብናል። የማኅበረሰብ አተያይ ትንተናን ለመስራት የሚከተሉትን ዝርዝሮች ከግንዛቤ ዉስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡-

            o  የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ለታሰበዉ ሕግ ያለቸዉን ቁርጠኝነት፤

            o   ለታሰበዉ ሕግ ከሚመለከተዉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት፣ ኤጀንሲ፣ወይም ሌላ የመንግስት አካል ድጋፍ ማግኘት፤

            o  ለታሰበዉ ሕግ የፖሊሲ ድጋፍ ያለዉ እና ከመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ጋር የተጣጣመ መሆኑን ማረጋገጥ፤

            o   በምክክሩ ላይ ተፅዕኖ ሊኖራቸዉ የሚችሉ ሕጎችን፣ፖሊሲዎችን ወይም የፍርድ ቤት ዉሳኔዎችን መመርመር፤

            o  በረቂቁ ላይ የማሕበረሰቡን እና የባለድርሻ አካላትን ፍላጎት፣ አተያይ፣እና ስሜት እና አቋም በመገምገም ለሚነሱ ክርክሮች ብሎም አለመግባባቶች ቀድሞ መዘጋጀት፤

            o    ጉዳዩ አከራካሪ እና የተወሰኑ አካላት ወይም የሚድያ የተለየ ፍላጎት የሚታይበት መሆኑን መገምገም፤ 

            o     ከባድ ምርጫዎች እና ማቻቻሎች መኖራቸዉን መገምገም እና 

            o     ከዚህ በፊት የመንግስት ተቋማት፣እና ባለድርሻ አካላት ያዘጋጇቸዉ ሪፖርቶች እና ቅስቀሳዎችን ማጥናት።

               6.3.የተሳትፎ እና የምክክር ዘዴዎችን መምረጥ (Selecting Consultation Tools)

 እንደ ረቂቅ ሕጎች ሁኔታ እና የሚፈጥሩት ተፅዕኖ እንዲሁም ምክክሩ የሚደረግበት ደረጃ የተለያዩ የተሳትፎና የምክክር ዘዴዎች በተግባር ላይ ሊዉሉ ይችላሉ። የተሳትፎዉ ወይም የምክክሩ ተሳታፊዎችን ማንነት፣ ያለንን በጀት፣ የምክክር ሂደቱን ስርዐት፣ እና በስራ ላይ የሚዉለዉን የመግባቢያ ዘዴ መሰረት በማድረግ የሚከተሉትን አምስት የተሳትፎና የምክክር ዘዴዎች መጠቀም ይቻላል። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባዉ ሁሉንም ወይም የተወሰኑትን ዘዴዎች መጠቀም የሚቻል ከመሆኑም በላይ በተቻለ መጠን ብዙዎቹን ዘዴዎች አጣምሮ መጠቀም ሕጎችን አሳታፊ በሆነ መልኩ ለማዉጣት አይነተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን ነዉ።

              6.3.1. የተሳትፎና የምክክር መድረኮችን ማዘጋጀት

 የተሳትፎና የምክክር መድረክ ተሳታፊዎች በአንድ አዳራሽ ዉስጥ በመሰብሰብ ሀሳባቸዉን የሚሰጡበት ስርዐት ሲሆን በኢትዮጵያ የተለመደዉ የተሳትፎና የምክክር ዘዴ ነዉ። የተሳትፎና የምክክር መድረኮች ሕግ አርቃቂዎች እና ባለድርሻ አካላት በአካል እንዲገናኙ ዕድል የሚሰጡ በመሆናቸው የባለድርሻ አካላትን ስሜት በተሻለ ደረጃ ለመረዳት ይረዳሉ። ይሁን እንጅ ከጊዜ እና ከበጀት እጥረት አንፃር ሁሉንም ባለድረሻ አካላት በተሳትፎና የምክክር መድረኮች እንዲሳተፉ ማድረግ አይቻልም። በኢትዮጵያ ሌሎች የአስተያየት መስጫ ዘዴዎች ያልዳበሩ በመሆኑ ሕግ በማዘጋጀት ሂደት የተሳትፎና የምክክር መድረኮችን ማዘጋጀት አስፈላጊ ነዉ።የተሳትፎና የምክክር መድረኮች ከመደረጋቸዉ በፊት ረቂቅ ሕጎች ወይም ሌሎች ለመድረኩ አስፈላጊ ሰነዶች ለተሳታፊዎች ቀድመዉ ሊደርሷቸዉ ይገባል።

             6.3.2. ረቂቅ ሰነዶችን እና ጥናቶችን ለሕዝብ አስተያየት ክፍት ማድረግ

 ረቂቅ ሕጎችን እና ጥናቶችን ለሕዝብ አስተያየት ክፍት በሆነ ማስታወቂያ በማዉጣት የህዝብ አስተያየትን መሰብሰብ ክፍት እና አሳታፊ የሆነ የተሳትፎና የምክክር ዘዴ ነዉ። ይህ አይነቱ ዘዴ ሁሉም ሰዉ ስለሕጉ መረጃ እንዲኖረዉ የሚያደርግ እና አስተያየት እንዲሰጥ ዕድል የሚሰጥ ነዉ። ረቂቅ ሕጎችን እና ጥናቶችን በተቋማት ድህረ-ገፅ በመልቀቅ ለማኅበረሰቡ ክፍት በማድረግ አስተያየቶችን መሰብሰብ ይቻላል። በሌላ በኩል ረቂቅ ሕጎችን እና ጥናቶችን ተነባቢ በሆነ ጋዜጣ በማዉጣት ሰዎች ሀሳባቸዉን በፖስታ ወይም በኢሜል እንዲልኩ ሊደረግም ይችላል። ነገር ግን ሰፊዉ ማኅበረሰብ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ባልሆነበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ ሀገር ይህን ዘዴ እንደ ብቸኛ የተሳትፎና የምክክር ዘዴ መጠቀም ተመራጭ አይደለም። ነገር ግን ከምክክር መድረኮች ጎን ለጎን ቢደረግ እጅግ አሳታፊ እና ተመራጭ ዘዴ ነዉ።

            6.3.3. ረቂቅ ሕጎችን እና ጥናቶችን ለባለድረሻ አካላት በመላክ አስተያየት መሰብሰብ

 ይህኛዉ የተሳትፎና የምክክር ዘዴ ሰነዶችን ለሚመለከታቸዉ እና ሕጉ ተፈፃሚ ለሚሆንባቸዉ አካላት በኢሜል ወይም በአካል በመላክ አስተያየታቸዉን በኢሜይል ወይም በአካል እንዲያስገቡ የሚደረግበት ዘዴ ነዉ።ይህ ዘዴ ከተደራሽነት አንፃር ለሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ክፍት አይደለም ይልቁንም በጣም አስፈላጊ ለሆኑ ባለድርሻ አካላት ሰነዶችን በማድረስ አስተያየት መሰብሰቢያ መሳሪያ ነዉ። በኢትዮጵያ ካለዉ የኢንተርኔት ተደራሽነት እና በምክክር መካተት ካለበት ሰፊ የማኅበረሰብ ክፍል አንፃር ይህን ዘዴ በብቸኝነት ከመጠቀም ይልቅ ከሌሎች ዘዴዎች ጋር መጠቀም ያስፈልጋል።

            6.3.4. ረቂቅ ሕጎችን እና ጥናቶችን ለአማካሪ ተቋማት በመላክ አስተያየቶችን መሰብሰብ

 አንድ ሕግ ከመዉጣቱ በፊት ረቂቅ ሕጉን እናጥናቱን በዚያ ሕግ ዙሪያ ለሚሰሩ ሀገር በቀል እና ዓለም አቀፍ የልህቀት ማዕከላት በመላክ ገንቢ የሆኑ አስተያየቶችን መሰብሰብ ጥራት ያለዉ ሕግን ለማዉጣት ዋና መሳሪያ ነዉ።የልህቀት ተቋማቱ በጉዳዩ ላይ የተለየ ዕዉቀት ያላቸዉ ባለሙያዎች ያሏቸዉ በመሆኑ ሕጉን በተሻለ ደረጃ ለማዳበር የሚያስችሉ ሀሳቦችን ሊሰጡን ይችላሉ። ይሁን እንጅ ይህ አይነቱን ዘዴ ስንጠቀም የባለሙያ ምክር ከመስጠት ባለፈ የተለየ ፍላጎት ያላቸዉ አካላት ሕጉ በፈለጉት መልኩ እንዲወጣ ተፅዕኖ እንዳያሳድሩ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

            6.3.5. መደበኛ ያልሆኑ ምክክሮችን ማድረግ

እነዚህ ምክክሮች በሕግ አርቃቂዎች እና በባለድረሻ አካላት መካከል የሚደረጉ መደበኛ ያልሆኑ እና ወጥነት የሌላቸዉ ምክክሮች ናቸዉ። እነዚህ ምክክሮች በሕግ ማርቀቅ ሂደት በማንኛዉም ጊዜ ሊደረጉ የሚችሉ ሲሆን በስልክ፣ በደብዳቤ፣ ወይም መደበኛ ያልሆኑ ስብሰባዎችን በማድረግ ሊከናወኑ ይችላሉ። መደበኛ ያልሆኑ ምክክሮች ሌሎች ምክክሮችን የሚተኩ ሳይሆን ባለድርሻ አካላት ስለረቂቅ ሕጉ ያላቸዉን አተያይ እና ስሜት ለመገምገም የሚደረጉ ናቸዉ። የተሳትፎና የምክክር ዕቅድ በማዘጋጀት ሂደት ትክክለኛዉን የተሳትፎና የምክክር ዘዴ ለመምረጥ የሚከተሉትን ከግምት ዉስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡-

      o  የተለያዩ የተሳትፎና የምክክር ዘዴዎችን በመዘርዘር በታሰበዉ ሕግ ላይ በሚደረግ ህዝባዊ ተሳትፎና ምክክር ጥቅም ላይ ቢዉሉ የሚኖራቸዉን ጥቅም እና ጉዳት ማመዛዘን፤

o  ተስማሚ የሆኑትን ዘዴዎች ለመምረጥ ባለድረሻ አካላትን ማማከር፤

o  በሕጉ ላይ የተለያየ ፍላጎት ያላቸዉ ቡድኖች በአንድ የምክክር ወይም የተሳትፎ መድረክ መሳተፍ አለባቸዉ ወይስ ለተለያዩ ቡድኖች የተለያዩ መድረኮችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል የሚለዉን መወሰን፤

o   በጉዳዩ ላይ ስምምነት ላይ መድረስ የምክክሩ ዓላማ ነዉ ወይስ አይደለም የሚለዉን መወሰን፤እና

o    የምንመርጠዉ የተሳትፎ ወይም የምክክር ዘዴ ከሕጉ ስፋት እና ተፅዕኖ አንፃር የሚመጥን መሆኑን ማረጋገጥ።

     6.4.      የሚያሰራ የጊዜ ሰሌዳ መቅረፅ

አንድ የተሳትፎ ወይም የምክክር ዕቅድ ምክክሩን ዕዉን በማድረግ ሂደት የሚሰሩ ስራዎችን ዝርዝር (set
of millstones)
እና የሚሰሩበትን ዝርዝር ጊዜያት የሚገልፅ የጊዜ ሰሌዳ ሊያካትት ግድ ይላል። የተሳትፎና የምክክር የጊዜ

ሰሌዳዎች ያልታሰቡ ሁኔታዎችም ጭምር ቢፈጠሩ ማስተናገድ የሚችሉ እና በቂ ጊዜ የሚሰጡ መሆን አለባቸዉ። የጊዜ ሰሌዳዎች ለተሳትፎዉ ወይም ለምክክሩ የሚያስፈልጉ እንደ ሆቴል እና የመሳሰሉ ግብዐቶችን ለማሟላት

የዉይይት ሰነዶችን ለማዘጋጀት እና ተሳታፊዎችን ለመጥራት እና ለተሳታፊዎች የዉይይት ሰነዶች ደርሰዋቸዉ ተዘጋጅተዉ የሚመጡበትን ጊዜ ከግምት ዉስጥ ያስገቡ መሆን ይኖርባቸዋል። የጊዜ ሰሌዳዎች የሚከተሉትን ከግምት

ዉስጥ በማስገባት ሊቀረፁ ይገባል፡-

        o  በዓላትን እና የተሳታፊዎችን የስራ ጫና ከግምት ዉስጥ በማስገባት ተሳትፎዉ ወይም ምክክሩ የሚደረግበትን ምቹ ቀን መምረጥ፤

        o  ጨረታዎችን ለማጠናቀቅ፣ ሰነዶችን ለማዘጋጀት፣ እና ተሳታፊዎችን ለመጥራት የሚያስፈልገዉን ጊዜ መወሰን፤

        o  በታሰበዉ የጊዜ ሰሌዳ ወሳኝ የመንግስት አካላት እና ባለድርሻ አካላት መገኘት የሚችሉ መሆኑን ማረጋገጥ፤

        o   ለተሳትፎዉ ወይም ምክክሩ የሚያስፈልጉትን ቀናት/ቀን/ሰአታት ብዛት መወሰን፤

        o   ተሳታፊዎች የተላኩላቸዉን ሰነዶች ለማንበብ እና አስተያየታቸዉን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጋቸዉን ጊዜ መወሰን፤

        o   በተሳትፎዉ ወይም ምክክሩ የሚቀርቡ ሰነዶችን ለማዘጋጀት የሚያስፈልገዉን ጊዜ መወሰን፤

        o  ተሳትፎዉ ወይም ምክክሩ ከተደረገ በኋላ ተሳታፊዎች የሰጧቸዉን ሀሳቦች በሰነድ መልክ በማዘጋጀት ለተሳታፊዎች መልሶ ሪፖርት ለማድረግ የሚያስፈልገዉን ጊዜ መወሰን፤እና

        o   በተሳትፎዉ ወይም ምክክሩ ቀን የሚኖሩ መርሀ ግብሮችን ከነጊዜ ገደባቸዉ ከፋፍሎ ማስቀመጥ።

        6.5.ተሳታፊዎችን መምረጥ

 በተሳትፎዉ ወይም ምክክሩ የሚሳተፉ አካላትን የመመልመያ መስፈርት ማዘጋጀት ተሳትፎ ወይም ምክክር በማድረግ ሂደት ዉስጥ ወሳኙ ስራ ሲሆን ማንኛዉም የተሳትፎ ወይም የምክክር ዕቅድ ሊያካትተዉ የሚገባ ዝርዝር ነዉ። የተሳታፊዎች የምልመላ መስፈርቶች እንደ ሕጎች አይነት የሚለያዩ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ተሳታፊዎች ባላቸዉ ሙያዊ ወይም አካባቢያዊ ዕዉቀት የሚመረጡ ሲሆን በሌሎች ሁኔታዎች ደግሞ ሕጉ ተፅዕኖ የሚያሳድርባቸዉ አካላት ይመረጣሉ። ስለሆነም የተሳታፊ መመልመያ መስፈርታችን እንደ ሕጉ ሁኔታ ተስማሚ ሆኖ ሊዘጋጅ ይገባል። የመመልመያ መስፈርቱ እያንዳንዱ ተሳታፊ የሚኖረዉን ሚና እና የሚያበረክተዉን አስተዋፅዖ ከግምት ዉስጥ ማስገባት ያስፈልጋል። የመመልመያ መስፈርታችን በተቻለ መጠን አካታች ሊሆን የሚገባዉ ሲሆን የተለያየ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ እና የማኅበራዊ ደረጃ ያላቸዉን የህብረሰብ ክፍሎች ተወካዮች ሊያካትት ይገባል፡፡ ባጠቃላይ የምክክር ተሳታፊዎችን ለመምረጥ የሚከተሉት መስፈርቶች ስራ ላይ መዋል ይገባቸዋል፡-

        o  የተሳታፊዎችን ብዛት ካለዉ በጀት አንፃር መወሰን፤

         በረቂቅ ሕጉ ተፅዕኖ ሊደርስባቸዉ የሚችሉ አካላትን እና ሕጉን የሚያስፈጽሙትን ተቋማት መለየት፤

        o  በታሰበዉ ሕግ ዙሪያ ልዩ ዕዉቀት እና ፍላጎት ያላቸዉን ባለሙያዎች እና ሙሁራን መለየት፤

        o  በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ከዚህ ቀደም የተሳተፉ ባለድርሻ አካላትን መለየት እና ላልተሳተፉት ቅድሚያ መስጠት፤

        o  በምክክሩ ሊወከሉ የሚገባቸዉ ክልሎችን፣ አካባቢያዎችን እና ተቋማትን መለየት እና መወሰን፤

        o    የሚመለከታቸዉን አካላት ለመለየት ከመንግስት ተቋማት እና ወሳኝ ከሚባሉ ባለድርሻ አካላት መሪዎች ጋር መነጋገር፤

        o    የመለመልናቸዉ ተሳታፊዎች በምክክሩ ላይ መገኘት የሚችሉ መሆኑን ማረጋገጥ፤

        o     አስፈላጊ ተቋማትን እና ግለሰቦችን ለመለየት የድህረ-ገፅ ፍለጋ ማድረግ፤

        o   ተሳታፊዎች ከተለዩ በኋላ ለተሳታፊዎች የጥሪ ደብዳቤ መላክ፤

        o    በተቋሙ ድህረ-ገፅ ላይ ስለምክክሩ ማስታወቂያ ማዉጣት፤እና    

        o    እንደነገሩ ሁኔታ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዎ ወይም በጋዜጣ ማስተዋወቅ።

       6.6.      የሚያሰራ በጀት መመደብ

 ማንኛዉም የተሳትፎ ወይም የምክክር ሂደት ዕዉን ይሆን ዘንድ ከፕሮጀክቱ ስፋት እና ክብደት ጋር የሚመጣጠን ገንዘብ፣ የሰዉ ሀይል እና ጊዜ መመደብ ግዴታ ነዉ። ምክክሩን ዕዉን ለማድረግ የሚያስፈልጉ የመግባቢያ (communication) የአቅርቦት እና መጓጓዣ፣ የሰነድ ዝግጅት፣የመድረክ መሪዎች፣ አቅራቢዎች፣ አስተባባሪዎች፣የሆቴል እና የማቴሪያል እንዲሁም ሌሎች የተሳታፊወች ወጭወችን የሚሸፍን በጀት መመደብ ግድ ይላል። የበጀት ፕሮፖዛል ከመቅረፅ በፊት የሚከተሉትን ከግምት ዉስጥ ማስገባት ያስፈልጋል፡-        o  በዕጃችን ያለ እና ልንጠቀመዉ የምንችለዉ ገንዘብ መኖሩን በማረጋገጥ መጠኑን መወሰን፤

        o   ምክክሩ በሦሥተኛ ወገን አስተባባሪነት ሊደረግ የሚችል መሆኑን ወይም አለመሆኑን መወሰን፤

        o   ያለን ገንዘብ ለምናስበዉ የተሳትፎ ወይም የምክክር ስፋት እና መጠን በቂ መሆኑን ማረጋገጥ፤

        o    ሌሎች መንግስታዊ ወይም መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ለምክክሩ አስተዋፅዖ ሊያደርጉ የሚችሉ ወይም የማይችሉ መሆኑን ማረጋገጥ፤

        o   ሰነዶችን ለማዘጋጀት ኮንትራክተሮች የሚያስፈልጉ ወይም የማያስፈልጉ መሆኑን መወሰን፤

        o   ከሌሎች አካባቢ የሚመጡ ተሳታፊዎች ካሉ የጉዞ፣የምግብ እና የአልጋ ወጫቸዉን መወሰን፤

        o   ለምክክሩ የሚያስፈልጉ እንደ ሆቴል፣የመሰብሰቢያ አዳራሽ እና የፅህፈት መሳሪያዎችን ወጪማ ስላት እና መወሰን፤

        o    ተሳታፊዎችን ለመጥራት የሚያስፈልጉ ወጪዎችን መወሰን፤

        o    ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸዉ እና ተጨማሪ ወጪ የሚያስወጡ ተሳታፊዎችን ቁጥርመወሰን እና ወጪዉን ማስላት፤ እና

        o   መጠባበቂያ ገንዘብ መያዝ። 

    
         6.7.ተከታታይ ግምገማ እና ስነዳ

ተሳትፎ ወይም ምክክሩን በማዘጋጀት ሂደት ችግሮች ካሉ ለማሰተካከል ይቻል ዘንድ ተከታታይ ግምገማዎች ማካሄድ አስፈላጊ ነዉ። ተሳትፎዉ ወይም ምክክሩ ከተደረገ በኋላ ደግሞ ሂደቱ አጠቃላይ ምን ይመስል እንደ ነበር እና የነበሩ ጉድለቶችን መገምገም ወደፊት የሚደረጉ ምክክሮችን በተሻለ ደረጃ ለመከወን ይረዳል። የተሳካ ግምገማ ለማድረግ አዘጋጆች ተሳትፎዉ ወይም ምክክሩ የታቀደዉን አላማ ከማሳካት አንፃር የነበሩትን እምርታዎች እና ጉድለቶች መመዘን የሚያስችል የግምገማ ማዕቀፍ ሊያዘጋጁ ይገባል። የግምገማ ማዕቀፉ እያንዳንዱን የተሳትፎና የምክክር ዕቅድ ይዘቶች ከማሳካት አንፃር የነበሩ ስኬቶች እና ጉድለቶችን መመዘን በሚያስችል መልኩ ሊዘጋጅ ይገባል። ይኸዉም የተሳትፎና የምክክር ዓላማ መግለጫ ከማዘጋጀት አንፃር፣ ተገቢዉን የተሳትፎ ወይም የምክክር ዘዴ ከመምረጥ አንፃር፣የተሳታፊዎች አመራረጥ እና ጥሪ፣ በጀት አመዳደብ፣ የማኅበረሰብ ግምገማ ሂደቶችን እና የጊዜ ሰሌዳ ከመቅረፅ አንፃር የተሰሩ ስራዎችን እና ጉድለቶችን መገምገም አስፈላጊ ነዉ።ተከታታይ ግምገማዎች ስኬቶችን ወደ ፊት የበለጠ ለመጠቀም ጉድለቶችን ደግሞ ለማረም ያግዛሉ።

ማንኛዉም የስራ ክንዉን ግምገማ ማዕቀፍ የሚከተሉትን ሊያሟላ ይገባል፡-

        

      o  የተሰሩ እና ያልተሰሩ ስራዎችን የሚዘረዝር የክትትል ሰነድ ማዘጋጀት፤

      o   የተመረጠዉ የተሳትፎ ወይም የምክክር ዘዴ ለማሳካት የታሰበዉን ግብ ዕዉን ማድረግ የሚችል ነበር ወይስ አልነበረም፤

      o   በዕቅዳችን ልክ ተሳታፊዎች ተሳትፈዋል ወይስ አልተሳተፉም፤ 

      o   ተሳታፊዎች ተሳትፎዉ ወይም ምክክሩ ጠቃሚ ነዉ የሚል ስሜት ተሰምቷቸዋል ወይስ አልተሰማቸዉም፤

      o     ያስቀመጥነዉ የጊዜ ሰሌዳ የምንፈልገዉን ግብዓት ለመሰብሰብ በቂ ነበር ወይስ አልነበረም፤

      o    ተሳታፊዎች በተጠበቀዉ ልክ በቂ ሀሳብ ሰጥተዋል ወይስ አልሰጡም፤

      o    የተሳትፎ ወይም የምክክር ሂደቱ በበቂ በጀት የተደገፈ ነበር ወይስ አልነበረም፤

      o    ተሳታፊዎች ምቹ በሆነ ዘዴ ጥሪ ተደርጎላቸዋል ወይስ አላተደረገላቸዉም፤እና

      o     አስፈላጊ ሰነዶች ከምክክሩ በፊት ቀድሞ ለተሳታፊዎች ደርሷቸዋል ወይስ አልደረሳቸዉም።

ሌላዉ በተሳትፎ ወይም በምክክር ሂደት ዉስጥ ዋነኛዉ ተግባር ከተሳታፊዎች የሚገኘዉን ግብዓት ቀጣይነት ባለዉ መንገድ መሰነድ ነዉ። አንድ ምክክር ለማከናወን የተዘጋጀዉ የተሳትፎ ወይም የምክክር ዕቅድ፣ የጥሪ ደብዳቤዎች፣ የበጀት ሰነዶች፣ ለዉይት የቀረቡ ሰነዶች፣ እና በቃለ ጉባኤ መልክ የተሰበሰቡ አስተያየቶች በተደራጀ ዘዴ ሊሰነዱ ይገባል። የተደራጀ ስነዳ የሕግ አወጣጥ ሂደቱ ተዐማኒ መሆኑን ከማስረዳቱም ባሻገር ወደፊት ሕጉን ለመረዳት እንደ አባሪ ሰነድ ሆነዉ ያገለግላሉ።

            7. በተሳትፎዉ ወይም በምክክሩ ሰዓት ሊደረጉ የሚገቡ ተግባራት

ተሳትፎ ወይም ምክክር ከመደረጉ በፊት መሟላት ያለባቸዉ ቅድመ ሁኔታዋች ከላይ በተገለፀዉ መልኩ ከተከናወኑ በኋላ የሚቀጥለዉ ተግባር ተሳትፎዉን ወይም ምክክሩን በዕቅዱ መሰረት ማከናወን ነዉ። አወያዮች እና አቅራቢዎች በተቻለ መጠን የሕግ ዝግጅቱ አካል የሆኑ እና ጉዳዩን በሚገባ የሚያዉቁ ባለሙያዎች መሆን ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም አወያዮች እና አቅራቢዎች ለተሳታፊዎች ሕጉን በሚመለከት ወቅታዊ፣ ግልፅ እና ጠቃሚ መረጃዎችን ለተሳታፊዎች ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ባጠቃላይ አወያዮች በምክክሩ ሰዓት የሚከተሉትን ተግባራት ሊፈፅሙ ይገባል፡-

o    የተሳታፊዎችን ማንነት እና የመጡበትን ተቋም መመዝገብ፤

o    በዕለቱ የሚኖሩ መርሀ-ግብሮችን እና የአቅራቢዎችን ማንነት የሚገልፅ ሰነድ ለተሳታፊዎች ማሰራጨት፤

o    ተሳታፊዎች የዉይይት ሰነዶች የደረሷቸዉ መሆኑን ማረጋገጥ፤

o    ሁሉም ተሳታፊዎች ያለልዩነት ተመሳሳይ መረጃ የደረሳቸዉ መሆኑን ማረጋገጥ፤

o   ረቂቅ ሕጉን በሚመለከት ወቅታዊ መረጃዎችን ግልፅ በሆነ ቋንቋ ለተሳታፊዎች ማቅረብ፤

o    ተሳታፊዎች ስለጉዳዩ ያላቸዉን የዕዉቀት ደረጃ በመገንዘብ በሚረዱት አገላለፅ ማቅረብ፤

o    መርሀ ግብሮች ቀድሞ በተቀመጠላቸዉ ሰዓት ዉስጥ እንዲጠናቀቁ ማድረግ፤

o    አወያዮች እና አቅራቢዎች አጭር ጊዜ በመዉሰድ ሰፊዉን መርሀግብር