የሕግ ማሻሻያ የስራ ክንዉን አጭር ዘገባ

የሕግ ማሻሻያ የስራ ክንዉን

አጭር ዘገባ

 

 ታህሳስ 15/ 2011

የኢ... ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሀገራችን ያለችበትን የለውጥ ሂደት ውጤታማነት ለማረጋገጥ የተለያዩ የተቋማትና የሕግ ማሻሻያ ስራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ የነዚህ ማሻሻያ ስራዎች ዓላማ ለውጡ ተቋዋማዊ፣ ሁሉን አቀፍና በጥናት በተደገፈ አካሄድ ተግባራዊ ተደርጐ የሕግ በላይነትና ፍትህ የሠፈነባት፣ ሰብዓዊ መብቶች የተከበሩባት፣ በዲሞክራሲያዊ አግባብ የምትመራ ሃገር መገንባት ነው፡፡ ይህን አላማ ለማሳካት የኢ... ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ከፍተኛ ልምድና ብቃት ያላቸውን አስራ ሶስት የሕግ ባለሞያዎች ያቀፈየሕግና ፍትህ ጉዳዮች አማሪ ጉባዔአቋቁሟል፡፡ ይህንን ጉባዔ ለመደገፍ ሥራውንም ለማሳለጥ የጉባዔው ፅህፈት ቤት ተቋቁሞ ባለሞያዎችም ተቀጥረዋል፡፡ ባለፉት አራት ወራት በጉባዔውና በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ /ቤት በትብብር የተሠሩ ሥራዎች አጭር ዘገባ እንደሚከተለው ነው፡፡

1.      አማካሪ ጉባዔው ከመቋቋሚያ መመሪያው በተጨማሪ የሚመራበትን ውስጠ ደንብ አፅድቆ  ተግባራዊ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም ጉባኤው የማሻሻያ ሥራውን የሚመራበት፣ አጠቃላይ አላማውንና የትኩረት አቅጣጫውን የሚያሳይ ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ አፅድቋል፡፡ እንዲሁም በጉባዔውና በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተግባራዊ በሚደረጉ የማሻሻያ ሥራዎች የባለድርሻ አካላትና የህዝብ ተሳትፎን ለማረጋገጥ የሚረዳ የህዝብ ተሳትፎ ስትራቴጂ ስነድ ተዘጋጅቶ በስራ ላይ ውሏል፡፡

2.      አማካሪ ጉባኤው ያቋቋመው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሕግ ማዕቀፍ የሥራ ቡድን፣ አሁን በሥራ ላይ ያለውንየበጐ አድራጐቶችና የማህበራት አዋጅ እንዲሁም የአዋጁን አተገባበርና ተያያዥ ጉዳዮችን የሚዳስስ ጥናት አካሄዶ፤ በጥናቱ ግኝት መሠረት ባቀረበው ምክረ ሃሳብ አዲስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሕግ ረቂቅ ተዘጋጀቶ፣ ረቂቁ ለሚኒስትሮች ምክር ተመርቶዋል፡፡ በዚህ ሂደት የጥናት ቡድኑ በመላው ሃገሪቱ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያወያየ ሲሆን ሕጉ የመደራጀት መብትን የተመለከቱ አለም ዓቀፍና አህጉራዊ፣ እንዲሁም ሕገ-መንግስታዊ መርሆዎችን ባገናዘበ መልኩ ተዘጋጅቷል፡፡ በቅርቡም ረቂቅ አዋጁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ የጸደቀ ሲሆን በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ በስራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

3.      በአማካሪ ጉባዔውና በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተቋቋመው የዲሞክራሲ ተቋማት የስራ ቡድን በቅድሚያ ለምርጫና ተያያዥ ጉዳዮች አትኩሮት በመስጠት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

  የስራ ቡድኑ፣

    በምርጫ ህጐችና በምርጫ አስፈፃሚ አካል ጋር ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን የሚለይ የዳሰሳ ጥናት አካሄዶዋል፡

    በዳሰሳ ጥናቱ በተለዩ አራት ርዕሶች ላይ ጠለቅ ያለ ጥናት አካሄዶዋል፡፡ (እነዚህም ርዕሶች የምርጫ አስፈፃሚው፣ ከምርጫ ጋር የተገናኙ ግጭቶች አፈታት፣ የምርጫ ስርዓትና፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመዘጋገብ ናቸው፡፡)

    የምርጫ ቦርድን አወቃቀር በተመለከተ በተደረገው ጥናት ላይ በመመስረት የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረኮች የተካሄዱ ሲሆን የምርጫ ቦርድን እንደገና ለማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶም ምክክር ተደርጎበታል፡፡ ይህ አዋጅ ረቂቅ በአጭር ጊዜ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚመራ ይጠበቃል፡፡

4.      የፀረ-ሽብር ህጉን ይዘትና አተገባበር ለማጥናት የተቋቋመው የሥራ ቡድን የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁንና አዋጁ በስራ ላይ የዋለበትን መንገድ የሚገመግም ጥናት አካሄዶ፣ በጥናቱ ላይ በመመስረት ረቂቅ አዋጅ ያዘጋጀ ሲሆን ረቂቅ አዋጁን የአማካሪ ጉባኤው በመገምገም ላይ ይገኛል፡፡ በጥናቱ ሂደት የሥራ ቡድኑ ተከታታይ የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረኮችን አካሄደዋል፡፡ አማካሪ ጉባኤው በቅርቡ ረቂቅ አዋጁን ፈትሾና ተገቢውን ማስተካከያ አድርጐ እንደሚጨርስ ይጠበቃል፡፡

5.      የሚዲያ ሕጐችን ለማሻሻል የተቋቋመው የጥናት ቡድን የኢትዮጵያን የሚዲያ ዘርፍ የህግ ማዕቀፍ የሚዳስስና ችግሮቹን የሚለይ ጥናት አካሄዶ በማጠናቀቅ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረኮች ካገኘው ግብዓት በመነሳት የሕግ ማርቀቅ ሥራ የጀመረ ሲሆን በጥቂት ወራት ውስጥ የሥራ ቡድኑ የሚዲያ የሕግ ማዕቀፉን የሚያሻሽሉ ረቂቅ አዋጆችን አዘጋጅቶ ለአማካሪ ጉባኤውና ለመንግስት እንደሚያስረክብ ይጠበቃል፡፡

 6.      በአማካሪ ጉባኤው የተቋቋመው የዳኝነት ጉዳዮች የጥናት ቡድን ስራውን የዳኝነት አካላት ነፃነትን በተመለከተ ጥያቄ በማያስነሳ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ ይችል ዘንድ ከአዲሶቹ የጠቅላይ ፍርድ ቤት አመራሮች ጋር በተደረገ ምክክር በጠቅላይ ፍርድ ቤት ስር መልሶ እንዲቋቋምና ስራውን እንዲሠራ ተደርጓል፡፡

7.      የህግ የበላይነት የተጠናከረበት የፍትህ ስርዓት እንዲኖር ጠንካራ የሆነ የሕግ ባለሞያዎች አስተዳደር የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ በመረዳት ይህንን ጉዳይ አጥንቶ የማሻሻያ ምክረ ሃሳቦች እንዲያቀርብ የተቋቋመው የሥራ ቡድን ጥናቱን ያጠናቀቀ ሲሆን በቅርቡ የጥናቱን ውጤት ይፋ በማድረግ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረኮችን ያዘጋጃል፡

8.      የአስተዳደርና የህግ ማውጣት ሥነ-ሥርዓትን ለማሻሻል የተቋቋመው የጥናት ቡድንም በተለይም ለአስተዳዳር ሥነ ሥርዓት ሕግ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ፣ እስከዛሬ በተለያዩ ተቋማት የተዘጋጁ ረቂቅ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት ሕጐችን በመገምገም ላይ ሲሆን በቅርቡ እነዚህን ረቂቆች መነሻ በማድረግ ረቂቅ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ለአማካሪ ጉባዔውና ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አንደሚያቀርብ ይጠበቃል፡፡

9.      በአማካሪ ጉባዔውና በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተቋቋመው ሌላው የሥራ ቡድን የወንጀል ፍትህ ሥርዓቱ ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸውን ፖሊሲ፣ ዐቃቤ ሕግና ማረሚያ ቤቶች ተቋማዊ ሁኔታ የሚገመግም የጥናት ቡድን ነው፡፡ ቡድኑ የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ ላይ ሲሆን፣ የማረሚያ ቤት ኮሚሽንን እንደገና ለማቋቋም የተዘጋጀውን ረቂቅ አዋጅ የሰብዓዊ
መብቶችንና ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ባገናዘበ መልኩ በመከለስ ሂደት እገዛ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ረቂቅ አዋጅ ተገቢው ክለሣ ተደርጐበት በቅርቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተዘጋጀው ረቂቅ የወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ የሰብዓዊ መብቶችን በሚባ በሚያስከብር መልኩ እንዲከለስ በማድረጉ ሂደትም ይህንን የሥራ ቡድን ድጋፍ በማግኘት በጥቂት ወራት ውስጥ የተሻሻለ ረቂቅ የወንጀል ሥነ-ስርዓት ሕግ ተዘጋጅቶ ለሚመለከተው አካል ይቀርባል፡፡

10.  ለረጅም ጊዜ በሥራ ላይ የቆየውን የንግድ ሕግ ለማሻሻል ከዚህ ቀደም የተጀመሪው ሥራ በቅርቡ ተጠናቆ ረቂቅ የንግድ ህግ የተዘጋጀ ቢሆንም ይህን አይነት ሕግ ለሃገሪቱ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ፣ በኮድ መልክ የሚዘጋጁ ህጐች ሊኖራቸው የሚገባውን ዘመን ተሻጋሪ ባህሪና የንግድ እንቅስቃሴ በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ድንበር ተሻጋሪ እየሆነ መምጣቱን ከግምት ባስገባ መልኩ ረቂቁን መከለስና ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ለዚህ ሥራ በአማካሪ ጉባዔው የተቋቋመው የስራ ቡድን ረቂቅ የንግድ ሕግ ኮዱን በዝርዝር እየገመገመ ሲሆን፣ ከዓለም ዓቀፍ ባለሞያዎች ጋር በመተባበር የክለሣ ሥራውን ለማካሄድ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ የተከለሰውና የተሻሻለው ረቂቅ የንግድ ሕግ በዓመቱ ማለቂያ ላይ ለሚመለከተው አካል ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

0 Comments

Leave a Comment